Oduu Haaraya

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ

ክፍል አንድ

የኦሮሞ ሕዝብ በሚኒሊክ ጦር ተወሮ፣ ሀገሩንና ነፃነቱን ካጣበት ጊዜ ጀምሮ ከመቶ ዓመታት በላይ ይነስ ይብዛ፣ ይጥበብ ይስፋ እንጂ በተናጠልም ሆነ በተደራጀ መልክ ያጣውን ነፃነቱንና ሀገሩን ለመመለስ ያልተቋረጠ ትግል ስያካሄድ እስከ ዛሬ ደርሷል። ስለዚህ የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት እንደ ተነሳ ወይንም እንዴት እንደጀመረ በሰፊው ማብራራት አስፈላጊ አይሆንም። ይህ ትግል የደረሰበት ደረጃና ዛሬ ምን ላይ እንደሚገኝም ለጠላትም ሆነ ለወዳጅ ግልፅ ስለሆነ፤ ይህንንም ጉዳይ በጥልቀት ማብራራት አስፈላጊ አይደለም።

ነገር ግን በጥልቀት መታየት ያለበትና እኔም በዚህ ላይ የራሴን ሀሳብ ለመግለፅ የምፈልገው ጉዳይ፣ ይህ ትግል ወዴት እየሄደ ነው? የሚለውን ጥያቄ ማየትና፤ እንደዚሁም በዚህ የነፃነት ትግል ውስጥ የነበሩት፣ አሁን ያሉትና ወደፊት ሊኖሩ የሚችሉት ፈተናዎችን በስፋት ማየት ነው። ይቆይ ይፍጠን፣ ይርዘም ይጠር እንጂ ይህ ትግል ወደ መጠናቀቂያው እንደተቃረበ ጥርጥር የለውም። ይሁን አንጂ ወዴት አንደሚያመራና የትኛውን ግብ እንደሚደርስ አሁን ማወቅ ያስቸግራል። ለምን ቢባል፣ ለዚህ ትግል ዓላማ የሚሰጠው ትርጉምና የትግሉ የመጨረሻ ግብ ምን መሆን እንዳለበት አከራካሪ ስለሆነ ነው። እዚህ ላይ ምን ማለት እንደፈለኩ እንደሚከተለው ለመግለፅ እሞክራለሁ።

እውነት እንናግር ከተበለ፣ ዛሬ በምንገኝበት ሁኔታ ውስጥ ቅድሚያ ማግኘት ያለበትና ቀዳሚው የትግሉ ዓላማ (primary objective) መሆን ያለበት ይህን ሰው በላ የወያኔ ስርዓት ገርስሶ፤ በሕዝባችን ላይ የተከፈተውን የዘር ማጥፋት ጦርነት ማብቃት ነው። አንድ ሰው እጅግ በጣም ከተራበ ያገኘውን ይበላል እንጂ፣ ይህ ወይንም ያ ይሻለኛል ብሎ አይመርጥም። የሕዝባችን ሁኔታም ይህንኑን ይመስላል። ሕዝባችን ዛሬ ሰላምና ነፃነት አጅግ ጥሞታል፣ እጅግ ርቦታል። ስለዚህ ቶሎ ይህንን ማግኘት አለበት። ከዚያ በኋላ ነው የረጅም ጊዜ ግቡን ለመድረስ ዕድልም ሆነ አጋጣሚ የሚኖረው።

ይህ ስለሆነ፣ የዚህ የነፃነት ትግል የመጨረሻው ግብ ምን መሆን አለበት ወይንም ደግሞ ምን መሆን ይችላል የሚለውን ጉዳይ አንስቶ ይህ ወይም ያ ነው ለማለት ባሁኑ ጊዜ አስፈላጊ አይመስለኝም። ይሁን እንጂ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ የምፈልገውና ይህ ሕዝብ የምመኘውን የምወስነውም ሆነ ከግብ የሚያደርሰው የትግሉ ባለቤት የሆነው ይኸው ሕዝብ ብቻ ነው። የትኛውም ድርጅትም ሆነ ቡድን ይህንን ልወስንለት አይችልም። ባጭሩ የራሱን ዕድል መወሰን ያለበት ይህ ሰፊው ሕዝብ ብቻ ነው ማለት ነው። የትኛውም ኃይል ይህንን ልወስንለት አይችልም።  የግል ፍላጎትም ሆነ ምኞት የዚህ ታላቅ ሕዝብ ፍላጎትም ሆነ ምኞት ሊሆን አይችልም። ይህ እውነታ ግልፅ መሆን አለበት።

እንግዲህ የትግሉን የመጨረሻ ግብ በሚመለክት ይህን ያህል ካልኩኝ በኋላ፤ የትግሉን ፈተናዎች በሚመለክት ኣንዳንድ ነገሮችን ማንሳት እሞክራለሁ። የነፃነት ትግሉን ፈተናዎች በሶስት ቦታ ከፍለን ማየት እንችላለን። አነሱም ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉት እና ነገ ሊታዩ የሚችሉ ፈተናዎች ናቸው። ትላንት የነበሩትን ፈተናዎች እዚህ በሰፊው ማንሳት አስፈላጊ ባይሆንም፣ ነገር ግን ካለፈው ለመማር ይረዳ ዘንድ እነዚህንም ትኩረት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ይሆናል።

የኦሮሞ የነፃነት ትግል የትላንትናዎቹ ፈተናዎች

የነፃነት ትግሉ ውስጥ የነበሩትን ፈተናዎች ሁሉ ማንሳትና ማብራራት ቀላል የማይሆን ጉዳይ ነው። ይህን ሰፊ ትንታኔ ለማድረግ የታሪክና የፖለቲካ ሙያም ይጠይቃል። ይሁን እንጂ የጉዳዩን ስፋትና ጥልቀት ለባለሙያዎቹ በመተው ያለኝን ሀሳብ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ለማብራራት እሞክራለሁ።

ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው፣ የመጫና ቱለማ የመረዳጃ ማህበር ምስረታ በፊት የነበረው ጊዜ በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ የጨለማ ጊዜ እንደነበረ ነው። ለምን ቢባል በመጡትን ባለፉት የሀበሾች ገዥ መንግስታት ስር በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የማንነት ማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድ ስለነበረ ነው። በዚህ የተነሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኦሮሞ ሕዝብ እንኳንስ መገናኘት ቀርቶ የጋራ ማንነታቸው ለመጥፋት መቃብር ጫፍ ላይ የደረሰበት ጊዜ ነበር። ስለዚህ በዚያን ጊዜ የነበረው ትልቁ ፈተና የኦሮሞን ማንነት እና ይህንን ትልቅ ብሔር ከጥፋት ማዳን ነበር። በዚህ ምክንያት በዚያን ጊዜ የነበሩት የኦሮሞ ብሔርተኞች ይህንን ጥፋት ተረድተው መፍትሔ ለመፈለግ ብለው ልዩ በሆነ ስልት የመጫና ቱለማን ድርጅት አቋቋሙ።

እዚህ ላይ ግልፅ ማድረግ የምፈልገው አንድ ጉዳይ ከመጫና ቱለማ ምስረታ በፊት የነበሩት እንደ ወሎና ባሌ የመሳሰሉትን ንቅናቄዎች መርሳቴ ወይም መዘንጋቴ ኣለመሆኑን ነው። የመጫና ቱለማን ምስረታ እንደ መነሻ የወሰድኩት ይህ ትግል በተቀናጀ መልክ መቸ እንደ ተጀመረና ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕዝብን ማንቃት የተጀመረው መቸ እንደሆነ ለመግለፅ ነው። ከዚያ በፊት የነበሩት ፈተናዎችም ከየትኛውም ፈተናዎች ያላነሱ እንደሆነ የታሪክ ሰዎች ማስረጃ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ የመጫና ቱለማ መስራቾችና መሪዎች ያሳለፉት ፈተናዎች ታሪክ የማይረሳው ጉዳይ ነው። በዚያን ጊዜ የነበሩት ታጋዮች ያስመዘገቡት ድሎች ናቸው ለዛሬው ትግልና እንደ እሳት እየነደደ ላለው ሕዝባዊ ንቅናቄ መሰረት የጣለው።

ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ምስረታ ጀምሮ እስክ 1991 ድረስ ኦነግን ስፈታተኑት የነበሩት ፈተናዎች በሁለት መንገድ ነበሩ። እነዚህም ባንድ በኩል ከጥላት ጋር በጠመንጃ መፋለም ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባችንን በይበልጥ ማስተማርና ማንቃት ነበር። በዚያን ወቅት በኦነግ ሲመራ የነበረው ትግል የተለያዩ ችግሮችንና ፈተናዎችን በማሻነፍ 1991 ትላልቅ ድሎችን ኣስመዝግቧል። ይህ ብቻ ሳይሆን በዚያን ጊዜ የተገኙት ድሎች ናቸው ለጠላት ያማይንበረከክና ጭቆናን መሸከም እንቢ ያለውን የቁቤ ትውልድን (Qubee Generation) የወለዱት።

ከ1991 በፊት ኦነግ ውስጥ የተለያዩ ፖለቲካዊ አመለካከትና አይዶሎጂ ቢኖሩም፣ ይህ የነፃነት ትግል መሪ የሆነው ድርጅት አንድነት ያለውና ጠንካራ ግንባር ነበር። እንዲዚያ ባይሆን ኖሮ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ የሚኮራባቸው ድሎች ባልተገኙ ነበር። በመሆኑም ኦነግ ዛሬ ተከፋፍሎ እቅሙም እንደ ያኔ ባይሆንም፣ አንግቦት የተነሳው ዓላማ በኦሮሞ ሕዝብ ልብና አእምሮ ውስጥ ነው ያለው ቢባል ሀሰት የሚሆን አይመስለኝም።  ኦነግ እንደ ድርጅት ቢዳከም እንኳን የተቋቋመለትና ይዞት የተነሳው ዓላማ ነው በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት እንዲያገኝ የሚያደርገው። ስለዚህ እንደ እኔ አመለካከት ይህ ድርጅት መሪዎቹ ስህተት ቢሰሩም፣ ድርጅቱ ሁለት ሶስት ቦታ ቢበታተንም፣ መሰደብ፣ መናቅ፣ መረገም የለበትም። ይህ ድርጅት ለኦሮሞ ያደረገውን መርሳት የለብንም ማለቴ ነው።

እስከ 1991 ድረስ በኦነግ የተመራው የነፃነት ትግል ታላላቅ ድሎችን ማስመስገብ ብቻ ሳይሆን የዚህ ትግል ግብ ምን መሆን እንዳለበትም ግልፅ አድርጎ ነበር። ከ1991 በኋላ የኦሮሞ ሕዝባዊ ንቅናቄ እስከ ጀመረበት እስከ 2015 ድረስ የኦሮሞ የነፃነት ጎራ (camp) መድከምና መቀዝቀዝ ብቻ ሳይሆን ስግብግብነት፣ ለስልጣን ሩጫ፣ ክህደት፣ የኦሮሞ ባሕልና ስርዓት ማጣት፣ መተቻቸት፣ መሳደብ፣ ትዕግስት ማጣት፣ በራስ መተማመን መጥፋት፣በጠላት ላይ የሚደረገውን ትግል ትተው እርሰ በርስ ላይ ጦርነት ማካሄድ ወዘተ በእጅጉ የታዩበት ወቅት ነበር። እነዚህ መጥፎ ልምዶች ዛሬም ቢሆን አልጠፉም። እነዚህ ደግሞ ለነፃነት ትግሉ ፈተናና እንቅፋት ከመሆንም ባሻገር፣ የትግሉንም ዓላማና ግብ ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ናቸው። ይህንን ጉዳይ “የኦሮሞ የነፃነት ትግል የዛሬዎቹ ፈተናዎች” በሚል ርዕስ በሚቀጥለው ክፍል ሁለት ፅሁፍ ውስጥ እናያለን።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

 

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ

ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ፅሁፍ ውስጥ ይህ የነፃነት ትግል ከየት እንደተነሳ፤ የተለያዩ ፈተናዎች እንዲሁም ብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ፣ ትላልቅ ድሎችን አንዳስመዘገበ ባጭሩ ተብራርቷል። እነዚህ ድሎች እንዳሉ ሆነው፣ ነገር ግን ከ1991 በኋላ የኦሮሞ ሕዝባዊ ንቅናቄ በ2015 እስከ ጀመረበት ጊዜ ድረስ የኦሮሞ የነፃነት ትግል ጎራ (camp) በተለያዩ ምክንያቶች ተዳክሞ እንደነበር፤ በዚህ በተፈጠርው ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ኣንዳንድ ለትግሉ እንቅፋት የሆኑት ነገሮች ተፈጥረውም እንደነበሩ በክፍል አንድ ፅሁፍ ውስጥ ተጠቅሰው ነበር። በዚህኛው ክፍል ሁለት ፅሁፍ ውስጥ ዛሬ ያሉትን የትግሉ ፈተናዎችን ለማብራራት እሞክራለሁ።

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ጠላቶች እነማን ናቸው፧

ይህ የነፃነት ትግል የውስጥና የውጭ ጠላቶች እንዳሉት ከማንም የሚደበቅ ጉዳይ አይደለም። የውጭውን ጠላት በሁለት ቦታ ከፍለን ማየት እንችላለን። እነዚህም፥

  • ከዚህ በፊት የኦሮሞን ሕዝብ ሲገዙና ሲጨቁኑ የነበሩ፤ ወደፊትም ይህንን ለማድረግና የድሮውን የጭቆና ስርዓት በተዘዋዋሪ መልሰው ሕዝባችን ላይ ለመጫን ምኞት ያላቸው ኃይሎች ሲሆኑ፤ ሌላው ደግሞ ይህንን የነፃነት ትግል ከተቻለው ለማጥፋት ካልሆነ ደግም ለማዳከም ከዚህም አልፎ በሕዝባችን ላይ የዘር ማጥፋት ጦርነት እያካሄደ ያለው የወያኔዎች ኃይል

 

  • የራሳቸውን ፍላጎትና የጂኦ ስትራቴጂ (geo strategy) ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ብለው ከላይ የተጠቀሱትን ኃይሎች የሚረዱ፤ ከኦሮሞ ነፃነት ትግል ጥርጣሬ ያላቸው የውጭ መንግስታት በተለይም በምዕራቡ ክፍል የሚገኙ የውጭ ኃይሎች ናቸው።

እንደኔ አመለካከት የውስጥ ጠላቶችን በሶስት ቦታ ወይም ቡድን ከፍለን ማየት እንችላለን። አነሱም፥

  • አንደኛ፥ በጠላትና ለጠላት የተገዙት፣ ለሆድ አደሮች፣ ከሃዲዎች፣ ሰርጎ ገቦችና ሰላዮች ሌት ተቀን ለጠላት የሚሰሩ ተላላኪዎች

 

  • ሁለተኛ፥ በቀጥታ ጠላት ባይሆኑም፣ ባካሄዳቸው ግን ግልፅ አቋም የሌላቸው፣ ግልፅ ዓላማና ግብ የሌላቸው፣ ትላንት ያሉትን ዛሬ የሚሽሩ፣ አውቀውም ይሁን ባለማወቅ (አብዛኛውን ጊዜ ግን እያወቁ) የዚህን የነፃነት ትግል ዓላማና ግብ በተሳሳተ መንገድ ለመግለፅ የሚጥሩ

 

  • ሶስተኛ፥ በየትኛውም ምክንያት ይሁን ለዚህ ትግል ምንም ደንታ የሌላቸው፤ በጠላት ፕሮፓጋንዳ በቀላሉ የሚሸነፉ፣ የሚነገራቸውን መቀበል እንጂ የራሳቸው የሆን ምንም አቋም የሌላቸው፤ የማንነት ችግር (identity crises) ያለባቸው ሲሆኑ እነዚህ በቀጥታ ጠላት ባይሆኑም በተዘዋዋሪ ለትግሉ እንቅፋት የሚሆኑ ስራዎችን የሚሰሩ ናቸው።

የኦሮሞ የነፃነት ትግል የዛሬዎቹ ፈተናዎች

እንግዲህ ከዚህ በላይ ባጭሩ እንደተገለፀው የትግሉ ጠላቶች (የውጭና የውስጥ) ሁለቱም ትላልቅ ፈተናዎች ናቸው። የውጭ ጠላት ግልፅ ስለሚሆን ይህንን በቀላሉ መለየትና መታገል ይቻላል። እነዚህን ለማሸነፍ ጠንካራ ኃይል ቢያስፈልግም እንኳ፣ ለይቶ መታገል አያስቸግርም ማለቴ ነው።

የውስጥ ጠላት ግን በእውነት በጣም አደገኛ ነው። ይህ ጉዳይ አንድ የኦሮሞን ተረት ያስታውሰኛል። እሱም ስለ እሳት ሲወራ ነው። ”Diina jedhanii iraa hin fagaatan; fira jedhanii itti hin dhiyaatan” ወደ አማርኛ ሲተረጎም፥ “ጠላት ነው ብለው አይርቁትም፣ ዘመድ ነው ብለው አይቀርቡትም”  የሚል ነው። የትግሉ የውስጥ ጠላቶች እንደ እሳት ናቸው ማለት ነው። ሲያቀርቧቸው የተለያዩ ተንኮልና ደባ እየሰሩ እውነተኛ ታጋዮችን ለመጉዳት ይሞክራሉ። ካልሆነም በርቀት የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ የታጋዮች ሞራል እንዲነካ ይጥራሉ። ጠላት ናቸው ተብለው እንዳይራቁ ደግሞ የራስ ዜጎች ናቸው። ታዲያ የራሱን ዜጋ ከሚክድ ዜጋ የበለጠ ምን ጠላት አለ??

በኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የሚኒሊክ ወታደሮች ኦሮሞን በኃይል ካሸነፉበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የኦሮሞ ጠላቶች በራሳቸው ኃይል ጠንካራነት በቻ ሳይሆን፣ ኦሮሞን በኦሮሞ በመያዝ ነው እስከ ዛሬ የደረሱት። ከሃዲና ተላላኪዎች ናቸው ለጠላት መንገድ እያሳዩ ሕዝባችንን ሲያስጨፈጭፉ የቆዮት፣ አሁንም ያሉት። ሲመጡና ሲያልፉ የቆዩት ጠላቶቻችን በሙሉ በውጭ ዕርዳታ ታንክና ተዋጊ አይሮፕላን ይኑራቸው እንጂ እውነት የትግሉ የውስጥ ጠላቶች ትብብር ባይኖር ኖሮ እስከ ዛሬ ድረስ የኦሮሞን ሕዝብ በጭቆና ስር አያቆዩም ነበር። የኦሮሞን የነፃነት ኃይል የሚያዳክሙትና የውጭው ጠላት እንዲጠነክር የሚያደርጉት የውስጥ ጠላቶች ናቸው። የኦሮሞ አንድነት አንዳይኖር ወይም እንዲዳከም የሚያደርጉትም የውስጥ ጠላቶች ናቸው እንጂ የውጭ ጠላቶች ጥንካሬ አይደለም። በርግጥ የውስጥ ጠላቶች በሚፈጥሩት ቀዳዳ በመጠቀም የውጭ ጠላት ውስጣችን ገብተው አንድነታችን አንዳይጠነክር ዕድል ያገኛሉ። ይህ ነው ለነፃነት ትግሉ እንቅፋትና ፈተና ሆኖ ትግሉም ከግቡ እንዲቆይ ያደረገው።

ስለ ኦሮሞ የነፃነት ትግል ግብ ማንሳቴ ካልቀረ፣ እስቲ ሌሎች ለትግሉ ዓላማም ሆነ ግብ ፈተና የሆኑትን ኣንዳንድ ነገሮች ለማንሳት ልሞክር። እጂግ በጣም የሚያሳዝን ነገር ዛሬ ኣንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ወይንም አክቲቪስቶች የሚያደርጉትን ብናይ፥ እነሱ ለኦሮሞ የነፃነት ትግል የሚሰጡት ፍቺ የሚያወናብድና ሕዝባችንን የሚያሳስት ሆኖ ይታያል። እንዴት ቢባል፥

  • አንደኛ፥ አገራችን ኦሮሚያ በወታደራዊ ኃይል እንደተያዘችና ዛሬም እንደዚሁ ተወራ እንዳለች የዘነጉ ወይንም ደግሞ እያወቁ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለመደበቅ የምሞክሩ ይመስላሉ ። ይህን በመመርኮዝ ወይም ከዚህ በመነሳት የኦሮሞ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ አንዳልሆነ አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ።
  • ሁለተኛ፥ የትግሉን መነሻ ወይም ዓላማውን በተሳሳተ መንገድ ለመግለፅ ከሞከሩ በኋላ በዚህ ግንዛቤ ላይ በመመስረት የትግሉም ግብ Abbaabiyyummaa Oromoo የኦሮሞ የአገር ባለቤትነትን ማረጋገጥ እንዳልሆነ አድርገው በማቅረብ፤ ኦሮሞ ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ነፃ ለማውጣትና ዲሞክራሲያዊ አገር ለማድረግ እንደሚታገል በማስመሰል የኦሮሞ የነፃነት ትግል ዓላማና ግብም ይኸው እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ።
  • ሶስተኛ፥ የኦሮሞ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጠይቅ የቆየውን መሰረታዊ ጥያቄ በተለይም ደግሞ የኦሮሞ ወጣቶች ቄሮ (Qeerroo) ሲያነሱት የቆዩትን ጥያቄዎች፣ አንግበው እየወጡ የነበሩት መፈክሮች ማስረጃ ሆነው ሳሉ፣ የኦሮሞ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው የፖሊሲ ሪፎርም (Policy Reform) ነው ባማለት የትግሉን ዓላማ እጅግ አሳንሰው በማቅረብ፣ ጥቃቅን ለውጦች ከተደረጉ የኦሮሞ ሕዝብ በነዚህ ተደስተው ትግላቸውን እንደሚያቆሙ አድርገው ሰውን ለማሳመን ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ።

ሌላው የሚገርም ነገር ዛሬ በይበልጥ የሚታሰር፣ የሚሰቃይ፣ የሚገደል፣ ከአገር የሚሰደድ፣ ንብረቱ የሚቀማ፣ ከቀዬውና መሬቱ የሚፈናቀል ወዘተ ኦሮሞ ሆነው እያሉ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሌሎች ሕዝቦች ዝምታን መርጠው በነበሩበት ወይንም ባሉበት ወቅት፣ ሳይጠሩ፣ ሳይጠየቁ ኦሮሞ ለመላው ኢትዮጲያ መሞት አለበት፤ መስዋዕትነት ከፍሎ ይህችን አገር ማኖር አለበት በማለት ለሰው ብለው ሕዝባችንን ለማስጨረስ ሕዝብን እያሳሳቱ ነው። እስቲ ልብ በሉ፥ ኦሮሞ አስከ ዛሬ ድረስ ለዚች አገር የከፈለውን ትልቅ መስዋዕትነት ለነፃነቱ ቢከፍል ኖሮ ዛሬ የአገሩ ባለቤት መሆን በቻለ ነበር።

እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች ሳነሳ እኔ በግሌ ከዚህች ኢትዮጲያ ከምትባል አገር ችግርም ሆነ ጥላቻ ኖሮኝ አይደለም። እኔ እያልኩ ያለሁት የዚህ የነፃነት ትግል ዓላማም ሆነ ግብ ወደማይሆን አቅጣጫ እንዳይወሰድ ይህንን መጠበቅና መከላከል ግዴታ ስለሚሆን ነው። አለበለዚያ በወደቁት ጀግኖቻችን ደምና አጥንት መቀለድ ይሆናል። ለሁሉም ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይና እውነታ ግን የኦሮሞ የነፃነት ትግል ዋናው ዓላማ (core objective) የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ማስቻል ነው።

በዚህ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሂደትም ሆነ ውሳኔ ውስጥ ከማን ጋርና እንዴት መኖር እንዳለበት የሚወስነው ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ነው። በነገራችን ላይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች በመሆኑ፣ ይህ ጉዳይ ለኦሮሞ በቻ ተብሎ የተቀመጠ ተደርጎ መታየትም ሆነ መወሰድ የለበትም።

በሚቀጥለው የፅሁፌ ክፍል ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከየት ተነስቶ ወዴት እየሄደ ነው?

– ትላንት የነበሩት፣ ዛሬ ያሉትና ወደፊት የሚኖሩት ፈተናዎች –

ብርሃኑ ሁንዴ

ክፍል ሦስት

በክፍል ሁለት ፅሁፍ ውስጥ የኦሮሞ የነፃነት ትግል የውስጥና የውጭ ጠላቶች በተለያዩ ቦታ ወይም ቡድን ተከፍለው ባጭሩ ተብራርተው ነበር። በተጨማሪም ኣንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች፣ ቡድኖችና ግለስቦች ወይንም አክቲቪስቶች ለኦሮሞ የነፃነት ትግል ዓላማ የተሳሳተ ፍቺ በመስጠት፤ በዚህ የተነሳ የትግሉም ግብ እንደዚሁ በተሳሳተ መንገድ እንዲታይ እያደረጉ መሆናቸውም በዚያው ፅሁፍ ውስጥ ተብራርቷል። በዚህ ክፍል ሦስት ፅሁፍ ውስጥ ክፍል ሁለት ውስጥ በተጠቀሱት የትግሉ የዛሬ ፈተናዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳዮችን ማንሳት እሞክራለሁ።

የኦሮሞ የፖላቲካ ድርጅቶች ዓላማዎች ይፃረራሉ ወይስ ይደጋገፋሉ?

ይህ ጥያቄ ከባድና የተወሳሰበ እንደሆነ ይገባኛል። ባሁኑ ጊዜ ይህን ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ አይሆንም የሚሉ ሊኖሩም ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ የነፃነት ትግሉ ጠላቶችና አጋሮቻቸው ይህንን ጥያቄ ጠምዝዘው እንደ ፕሮፓጋንዳ ተጠቅመውበት በኦሮሞ መካከል ችግር እንዳይፈጥሩ ይህንን ጉዳይ በጥንቃቄ ማየት በጣም ወሳኝ ነው። በሌላ በኩል ሲታይ ግን ዛሬ ያሉትን ችግሮቻችንን ካልተረዳን፤ ቤታችንን ዛሬውኑ ማፅዳት ካልጀመርን፤ ነገ ሌሎች ችግሮች ውስጥ መግባታችን ስለማይቀር፣ ይህ ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘ ወደፊት ኦሮሞና ኦሮሚያን አደገኛ ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል። ስለዚህ ፈርተው ያሉትን ችግሮች መደበቅ ወይም መሸፋፈን ሕዝባችንን ይጎዳል እንጂ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።

ከዚህ በላይ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ከመፈለግ በፊት፣ ባሁኑ ጊዜ በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር የሚገኙትን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በሁለት ትላልቅ ቡድኖች ከፍሎ ማየት ይቻላል። ኦሕዲድ (OPDO) እነዚህ ውስጥ ኣል ወይስ የለም? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ነገር ግን አዲሱ የዚህ ድርጅት አመራር ሕዝባዊነትን እያሳየ ቢሆንም ይህ ድርጅት ለአሁን ነፃ የሕዝብ ድርጅት ስላልሆነ፣ ይህንን ድርጅት በዚህኛው ማብራራዬ ውስጥ አልከትም። ወደፊት ግን ይህንን ድርጅት በሚመለከት ሀሳቤን ኣቀርባለሁ። ሁለቱ ዋና ዋናዎቹ ቡድኖች፥

 

  • የኦሮሞ የነፃነት ኃይሎች – እነዚህ የኦሮሞን ሕዝብና የኦሮሚያን ነፃነት እንደ ትግሉ ዓላማቸው አድርገው የሚታገሉና ግባቸውም ይህንኑን ለማረጋገጥ የሆኑ ኃይሎች ናቸው። እንዴት እየታገሉ እንዳሉ ሌላ ጥያቄ ስለሆነ፣ ይህንን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።

 

 

 

  • የኦሮሞ የዲሞክራሲ ኃይሎች – እነዚህ ደግሞ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት እንታገላልን የሚሉ ነገር ግን ግባቸው ከነፃነት ኃይሎቹ ግብ ወዲህ የሚሆን ማለትም የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነቱን ካገኘ፣ በዚህች ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ የኦሮሞ ጥያቄ ሊመለስ ይችላል የሚሉ ኃይሎች ናቸው።

 

እዚህ ላይ ዲሞክራሲ የሚለውን ቃል የጨመርኩበት ምክንያት፣ የነዚህ B) ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች የትግላቸው ዓላማ እንደነሱ አባባል ኢትዮጵያን የዲሞክራሲ አገር ለማድረግ ስለሆነ ነው እንጂ በ A) ውስጥ የሚገኙ የነፃነት ኃይሎቹ በዲሞክራሲ አያምኑም ለማለት አይደለም።

እንግዲህ ከላይ ባጭሩ እንደ ተገለፀው፣ ሁለቱም ኃይሎች በጋራ ያላቸው ዓላማ የኦሮሞን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ይመስለኛል። ይህንን የጋራ ዓላማ ካላቸው ደግሞ የትግል ዓላማቸው አይፃረርም ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ከኦሮሞ ሕዝብ ነው የተፈጠሩት፤ የዚህኑን ሕዝብ ስም ነው ኣንግበውም የተነሱት፤ ለዚሁ ሕዝብ እንቆማለን እያሉም ነው። ታዲያ አንድ የጋራ የሆነ ነገር እንደ አጭር ጊዜ የትግል ዓላማ ይዘው በመተጋገዝ አብረው ከመስራት ይልቅ እርሰ በርስ መተቻቸትና አንዱ ለሌላው እንቅፋት መሆን መጣር ከየት መጣ? ወይንስ የማያግባባቸው ሌላ ምክንያት አለ ማለት ነው? የነዚህ ኃይሎች ኣለመግባባት ደግሞ ለነፃነት ትግሉ ሌላ ፈተና ይሆናል። የራስን ቤት ማፅዳት ከዚህ መጀመር ስላለበት።

በሌላ መንገድ ሲታይ ግን፣ እንደኔ አመለካከትና ግንዛቤ እነዚህ ኃይሎች ዓላማቸው እንዲፃረር የሚያደርገው የነፃነት ትግሉ የመጨረሻ ግብ ነው ብዬ አስባለሁ። A) ውስጥ ያሉት ኃይሎች ስማቸው እንደሚያሳየው የኦሮሞን ሕዝብ ነፃነት ከማስገኘትም ባሻገር፣ የኦሮሚያን የወደፊት ዕጣ ፋንታ በኦሮሞ ሕዝብ እንዲወሰን የሚታገሉ ናቸውብዬ አምናለሁ። የራስን ዕድል በራስ/ለራስ የመወሰን መብትን መሰረት በማድረግ ማለት ነው። በነፃነት ኃይሎቹ አገላለፅ የኦሮሞ መሰረታዊው ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ በመሆኑ፣ በቅኝ ግዛት ስር ያለች አንድ አገር ደግሞ ከቅኝ ግዛት መውጣት አለበት ብለው ስለሚያምኑም ነው። የራሱን ዕድል በራሱ/ለራሱ የመወሰን መብት ደግሞ የማንኛውም ሕዝብ ተፈጥሮአዊ መብት ስለሆነ፣ ይህ አካሄድ ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ለኦሮሞ ሕዝብ ብቻ የተፈጠረ መብት ስላልሆነ ማለቴ ነው።

ኢትዮጲያ የዲሞክራሲ አገር ከሆነች የኦሮሞ ጥያቄ በዚህ ውስጥ ሊመለስ ይችላል የሚሉት B) ውስጥ ያሉት ኃይሎች ይህንን እንደ ትግላቸው ዓላማና ግብም ለማድረግ መብት ኣላቸው። ይሁን እንጂ የኦሮሞ የነፃነት ትግል ከኢትዮጲያ አመሰራረት ታሪክ ጋር ተያይዞ ከታየ፣ የኦሮሞ ሕዝብ እየቆሰለ እስከ ዛሬ የደረሰውን ቁስሉን አገሪቷን ዲሞክራሲያዊ አገር በማድረግ የሚድን ይመስላል? የሚለው ሌላ ትልቅ ጥያቄ የሚያነሳ ይመስለኛል። እውነት እንናገር ከተባለ ኢትዮጵያ የምትባል አገር በኃይል ከተመሰረተችበት ጊዜ ኣንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ለራሱ ምንም ፋይዳ ሳያገኝ ይህችን አገር ለማኖር ብሎ እንደ ኦሮሞ ከፍተኛ መስዋዕትነትን የከፈለ ሌላ ብሔርም ሆነ ሕዝብ በዚያች አገር ያለ አይመስለኝም። ይሁን እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ብድር ይህ ሆኖ፣ ይኸው ዛሬ የዘር ማጥፋት ጦርነት ተክፍቶበት በመላው ኦሮሚያ ሕዝባችን እየደማ ነው ያለው። በመሆኑም ካሁን በኋላ ለኦሮሞ ምን ይመጣል ብለው ራስን መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።

ስለዚህ ትልቁ በኦሮሞ የነፃነት ጎራ (camp) ውስጥ ያለው ችግር የዚህችን አገር ሁኔታና የኦሮሞን ታሪክ ጎን ለጎን ይዘው ማይትና መገንዘብ ኣለመቻል ይመስለኛል። የነፃነት ትግሉ መንስዔ ወይም የኦሮሞ ብሔራዊ መሰረታዊ ጥያቄ ምን አንደሆነ በዚህ ላይ መግባባት እስከ ሌለ ድረስ፤ በትግሉ የጋራ ዓላማና ግብ ላይ መስማማት  እስከ ሌለና የጋራ የትግል ስልትና እስትራቴጂ ማውጣት እስካልተቻለ ድረስ የዚህ የነፃነት ትግሉ ፈተናዎች እየበዙና እየሰፉ ነው የሚሄዱት እንጂ የሚቀንሱ አይመስሉም። ይህ የአለመግባባት ችግር እንደዚሁ ከቀጠለ ደግሞ፣ የራሳችንን ቤት ማፅዳት ቀርቶ ያለውም የመፍረስ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል ማለት ነው። በዚህ እጅግ በጣም በተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ ድንገት አንድ ለውጥ እንኋን ቢመጣ፣ ስላልተዘጋጀንበት አሁንም ሌላ ዕድል ሊያመልጠን ይሆናል ማለት ነው። ያዚህች አገር ታሪክ እንደሚያሳየው ሁል ጊዜ አንድ ለውጥ ሲመጣ ያልታሰበና ያልተጠበቀ ኃይል በዚህ አጋጣሚ እንደሚጠቀም ነው።

እውነታው ይህ ስለሆነ ዛሬ ካሉት የነፃነት ትግሉ ፈተናዎች ውስጥ አንዱና ትልቁ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ የሆነ ዓላማና ግብ ማጣታቸው መሆኑ ለሁሉም ግልፅ መሆን አለበት። ድርጅቶቻችን የሚፃረሩ ዓላማና ግብ አንግበው እስከሄዱ ድረስ ለሕዝባችን ውዥንብር የመፍጠሩ ጉዳይ እንዲሁ ይቀጥላል ማለት ነው። በዚህ መንገድ በሚፈጠሩት ሁነታዎች ውስጥ ጥሩ ዕድልና ትርፍ የሚያገኙት የነፃነት ትግሉ ጠላቶች ብቻ ናቸው እንጂ ሕዝባችን ከዚህ የሚያገኘው ፋይዳ የለም። ታዲያ ለምንድነው ይህንን እውነታ የማንገነዘበው? ለምንድነው የራሳችንን ችግር መፍታት ትተን የባዕድ ጎራ ሄደን የሌሎችን እገዛ የምንጠይቀው? የኦሮሞን አቅም ንቀን ነው ወይስ በራሳችን መተማማን ኣንሶን ነው? የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ለውጥ ለማምጣት አንድነትም ሆነ አቅም (capacity) አንዳለው ለዓለም እንኳን ባሳየበት ወቅት፤ የዚህን ትልቅ ሕዝብ ኃይል ለራሱ ነፃነት እንዲያውል ከማስቻል ውጭ ለሌሎች ነፃነት ብሎ መስዋዕትነት እንዲከፍል ለምን እናደርጋለን? ኦሮሞ ራስህን ጠይቅ/ራስሽን ጠይቂ!!!

በኦሮሞ የነፃነት ትግል ጎራ ያሉት ችግሮች በሌላ መንገድ ሲታዩ ደግሞ፣ የትግሉ ዓላማና ግብ ልዩነት ብቻ አለመሆኑንም መረዳት ይቻላል። እንዴት ቢባል፣ አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ዓላማና ግብ ያላቸው የኦሮሞ ድርጅቶችም እኮ አንድነት ፈጥረው ኃይላቸውን ሲያጠናክሩ ኣልታዩም። ይህ ለምን ሊሆን ቻለ? ከኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት የሚበልጥ የግል ፍላጎት ነው ያለው? እነዚህን ጥያቄዎችና እንዲሁም ከዚህ ጋር የሚገናኙትን ጉዳዮች በሚቀጥለው የፅሁፌ ክፍል ውስጥ እናያለን።

ተመልሰን እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ።

 

Check Also

faannoo

OROMO CIVILIANS CONTINUE TO BE TARGETED BY FANO MILITIA

Amhara Fano continued to attack Oromo civilians. In this latest incident, at least 17 people …