ድምፃችን ይሰማ
የዛሬ አርብ ግንቦት 8 የጠዋቱ የችሎት ሪፖርት
አርብ ግንቦት 8/2006
ዛሬም እንደተለመደው ሁሉ ኮሚቴዎቻችን 3፡05 ላይ በግቢው ተገኝተው የነበሩ ቢሆንም ችሎቱ የተጀመረው ግን 4 ሰዐት ላይ ነበር፡፡ ከአቃቤ ህጎቹ ሁለቱ ችሎት ከተሰየመ በኋላ ነበር የደረሱት፡፡ ዛሬ ለመመስከር ችሎት የተገኘው አወሊያ ኮሌጅ ተማሪ የነበረው ቶፊቅ ወንዴ ይመር ሲሆን ካሁን በፊት ተበይኖ እንደነበረው በአንድ ጊዜ አንድ ጭብጥ ላይ ለመመስከር እንዳይችል ግን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ከክርክር በኋላም በትእዛዙ መሰረት በሁለት ጭብጦች ላይ በአንድ ጊዜ እንዲመሰክር ተደርጎ ድንቅ ምስክርነቱን አቅርቧል፡፡ ገና ሲጀምር ዳኞች የተከሳሾችን ስም በቃሉ እንዲጠቅስ ሲያስገድዱ መታየታቸው የችሎቱን ተከታታዮች ያስገረመ ክስተት ነበር፡፡
ተማሪ ቶፊቅ በሰጠው ምስክርነት በርካታ ነጥቦችን አንስቷል፡፡ ሶስት የወቅቱ መጅሊስ ሰዎች የኮሌጁን ሀላፊዎች ከማናገራቸው በፊት ተማሪዎችን ሰብስበው ካሪኩለም ሊለወጥ መሆኑን የነገሯቸው መሆናቸውንና ‹‹ለምን ከኛ በፊት የኮሌጁን ሀላፊዎች አላናገራችሁም?›› የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድቷል፡፡ ቆይቶ ከ85 ላላነሱ አስተማሪዎች አዳሪ ተማሪዎች የስንብት ደብዳቤ በስማቸው እንደመጣና የተሰጣቸው ሰበብም ‹‹ካሪኩለም ይለወጣል›› የሚል መሆኑን አብራርቷል፡፡ ‹‹አወሊያ ውስጥ ያሉ ሃላፊዎችን በየደረጃው አናግረን መፍትሄ ስላላገኘን በጠሩን መሰረት አቶ አህመዲን አብዱላሂ ጨሎን አናግረናል›› ያለው ተማሪ ቶፊቅ ‹‹አቶ አህመዲን ‹የመጣችሁበት ክልል ከየት ነው?› የሚል ጥያቄ ጠይቀውን ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከጉራጌና ከሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች መሆኑን ስንነግራቸው ‹አስቸጋሪ ከሆነ ክልል ነው የመጣችሁት› የሚል አስገራሚ መልስ ሰጥተው ‹አገራችሁ ሂዱና ካሪኩለም ከተለወጠ በኋላ እንጠራችኋለን› ብለው እንዳሰናበቷቸው ተናግሯል፡፡
ተማሪ ቶፊቅ እንዳስረዳው ሁሉም ከየክልሎች መስፈርቶችን አልፈው የመጡ አዳሪ ተማሪዎች በመሆናቸው መሄጃ እንዳልነበራቸውና ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረዋል፡፡ በሂደትም የአስተዳደር ቢሮዎች መታሸግ እንደጀመሩና የተቃውሞ ጥያቄዎች ቀርበው የመጅሊሱ ጸሀፊ መጥተው ተማሪዎች ላይ ማሾፋቸውን፣ እንዲሁም የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ዲንቃም ከኋላ ሆነው ‹‹ሳቅባቸው›› እያሉ ጸሀፊውን እንዲያሾፍባቸው ሲነግሩ መስማቱን መስክሯል፡፡ የተማሪዎች ተቃውሞ ተጠናክሮ ኮሚቴ እከመምረጥና ህዝበ ሙስሊሙን ማሳተፍ ደረጃ የደረሰበትን ዝርዝር ሂደትም በሰፊው አስረድሯል፡፡
ተማሪ ቶፊቅ ምስክርነቱን ባቀረበበት ወቅት አቃቤያነ ህግጋት፣ በተለይም አቶ ቴዎድሮስ ‹‹እንደምስክር እንጂ እንደአክቲቪስት አትናገር›› በሚል በተደጋጋሚ ሲያቋርጡት የነበረ ሲሆን ጠበቆችንም ‹‹ዲሲፕሊንድ ይሁኑልን፤ መሪ ጥያቄ አይጠይቁ›› ብለው እስከመናገር ደርሰዋል፡፡ ጠበቆች ‹‹ለቀረበብን ዘለፋ መልስ የመስጠት እድል ይሰጠን›› ቢሉም ፍቃድ አልተሰጣቸውም፡፡ በመጨረሻም ከሰዓት በኋላ ለመስቀለኛ ጥያቄ ቀጠሮ ተይዞ ችሎቱ ተጠናቋል፡፡
የሐሰት ከስ አይገዛንም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
Check Also
Dhaabbanni Itiyoo-telekoom olaantummaa dhalattoota saba tokkoo qofaan kan dhuunftameedha
Ragaan sanadaa loogummaa fi olaantummaa dhalattoota saba tokkootiin dhuunfatamuu Itiyoo-telekoom saaxilu OMN harka seenuu itti …