Oduu Haaraya

የኦሮሞ ህዝብን ለከፋ ጉዳት በመዳረግ ለራሳቸው እድገትን የመመኘት የጨቋኞች የዘመናት ኣካሄድ በኣሁኑ ትውልድ ፍጻሜ እንዲያገኝ መስራት የዜግነት ግዴታ ነው!

የኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግስት ከ24 ዓመታት በፊት የህዝቦችን መብት ባለማክበሩ ከስልጣን ተወገደ። ለወቅቱ ወታደራዊ መንግስት ቀዳሚውና ወሳኙ ጉዳይ በሃይል የተመሰረተችዋን ሃገር በጦር ሃይል ማሰንበት ነበር። ኢምፓዬሪነቷን ለመሸፋፈንና ለም ሃገር መሆንዋን ለማሳየት፡ በሃሰት የሶሻሊስታዊ ካባ ስር ደበቃት። ይመራበት በነበረው በዚህ ርዕዮተ-ዓለም(ኣይዲዮሎጂም) የኢትዮጵያን ኢምፓዬር ኣንድነት ለማስጠበቅ ለራሱ በገባው ቃል ጦርነት ኣውጆ፡ ለረጅም ዓመታት ጦርነቱን ሲያካሄድ ከሰነበተ በኋላ ራሱ በጦርነት ተወገደ። የኢትዮጵያን ኢምፓዬር የሱን ምኞት እውን የሚያደርጉለትን ልጆቹን ለማውረስ ያደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቶ የዚያ ወታደራዊ መንግስት ምዕራፍ በውድቀቱ ተቋጨ።

24 ዓመታት ወደኋላ መለስ በማለት በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ሲታይ፡ የዚያ ወታደራዊ ኣምባገነን መንግስት ዓላማ በኣንድነት፤ እኩልነትና ሶሻሊዝም ስም፡ የጭቆና ስርዓትን ማሰንበትና ማስጠበቅ መሆኑን መረዳት ይቻላል። በዚያ ዘመን እዉን እንደሆነ ሌተቀን ሲለፈፍ የነበረው እኩልነት ከቅጥፈትና ማታለል ኣልፎ በስራ የተረጋገጠ ኣልነበረም። የፖለቲካና ፓርቲ ስርዓት ኣስተዳደሩን ለመምራት የተዘረጋው ስርዓትም ኣምባገነናዊ፤ የመብት ጥያቄ ያላቸውን ህዝቦች ያፈነ፤ የግለሰብና የቡድን መብቶችን የነፈገ እንደነበር ይታወቃል። ወታደራዊው ጁንታ የህዝቦችን መብት የጦር ሃይል ወይንም በጠብመንጃ ኣፈሙዝ ለማፈን ጥረት ቢያደርግም፡ ህዝቦች የተነፈጉትን መብት መጎናጸፍ ፍላጎታቸው ስለነበረ የወታደራዊውን መንግስት ዓላማ ተቃውመው የነጻነትና ዲሞክራሲ ትግልን በመደገፍ ለመብታቸው በመታገል ያንን ኣምባገነን ወታደራዊ መንግስት ከስሩ መንግለው ጣሉት።
በኢትዮጵያ ከወታደራዊው መንግስት በኋላ ወደ ስልጣን የወጣው ቡድን ትግል ላይ በነበረበት ወቅት ለህዝቦችን መብትና ለዲሞክራሲ እንደሚታገል ሲለፍፍ የቆየ በመሆኑ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ቀደም ብሎ ከነበረው ወታደራዊ መንግስት ብዙም ያልራቀ ዓላማና ግብ ያለው መሆኑን ለመገንዘብ ግዜ ኣልወሰደም። ያለው ልዩነት የኢትዮጵያ ኢምፓዬርን ለማስጠበቅ የዘረጉት ፖሊሲና የሚከተሉት ስልት ነው። የደርግ መንግስት በሶሻሊስታዊ ርዕዮተ-ዓለም ለማስጠበቅ ሲጥር የወያኔ መንግስት ደግሞ በዲሞክራሲና ፌዴራላዊ ስርዓት ስም፥ ለብሄሮችና ህዝቦች መብት እውቅና እንደሚሰጥና እንደሚያከብር ኣስመስሎ እራሱን በማቅረብ የኣናሳ ቡድኑን የበላይነት ለማስጠበቅ ጥረት ሲያደርግ ይታያል።

ዛሬ በሃገሪቷ ብሄሮችና ህዝቦች ውስጥ የወያኔን ስርዓት የማይጋፈጡትና የማይቃወሙት ኣሉ ቢባል፡ ከተዘረጋው ስርዓት ጥቅም እያገኙ ያሉ ብቻ ናቸው። ከነዚህ ጥቂት ቡድኖች ውጪ ሁሉም የሃገሪቷ ህዝቦች መብቶቻቸው ኣንዳች ገደብ ሳይደረግበት እንዲከበሩላቸው ይሻሉ። ለዚህም በመታገል ላይ ናቸው። በተለያዩ የሃገሩቷ ኣካባቢዎች እየታዩ ያሉት የህዝቦች ተቃውሞና እርምጃዎች ለዚህ ኣብይ ምስክር ይሆናሉ። የብሄሮችና ህዝቦች ጥያቄዎች ኣጥጋቢና ትክክለኛውን ምላሽ እስካላገኙ ድረስም ተጠናክረውና ተፋፍመው የሚቀጥሉ ለመሆናቸውም ተጨባጭ ማስረጃ ይሆናሉ። ዛሬ ማንኛውም ህዝብ በውሸት ኣንድነት የማይታለልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ህዝቦች በኣንድነትና ዲሞክራሲ ስም እየተፈጸመ ያለውን ደባና ሴራ ለመለየት ኣይቸገሩም። ማን ለፍትሕ እንደቆመ፤ ማን የጭቆና ኣገዛዝና ዝርፊያን ለማስቀጠል ሲል በሃሰት እንደሚለፍፍና ማንስ ለስልጣን ጥማትና መልኩን የለወጠ የጭቆና ኣገዛዝ ለመዘርጋት እንደሚመኝ ህዝቦች ለይተው ኣያውቁም ኣልያም ኣይገነዘቡም ብሎ የሚያስብ ወይንም የሚያምን ካለ ህዝቡ ውስጥ የሌለ፤ የህዝቡን ሃሳብና ፍላጎት ለመስማትና ለማወቅ የማይፈልግ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ኢምፓዬር ውስጥ የብሄሮችንና ህዝቦችን መብት የሚያከብር ኣይነተኛ ለውጥ እስካልተገኘ ድረስ ኢትዮጵያ ከሁከት፤ ጭቆናና ዝርፊያ ኣትወጣም የሚባለውም ለዚሁ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከመቶ ዓመታት በላይ የኦሮሞ ህዝብ በሺዎች ከቀዬውና መሬቱ ተፈናቅሎ ሲባረር ኖሯል። በሰሜን ሸዋና ወሎ ውስጥ የተፈጸመው ለዚይ ቀዳሚው ማስረጃ ነው። በቀድሞውና በኣሁኑ መካከል ያለው ልዩነት፡ የቀድሞው «ማቅናት» በሚል ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ኣሁን በዘመነ-ወያኔ ደግሞ «በልማትና እድገት» ሽፋን የሚካሄድ መሆኑ ነው። የቀድሞው ስርዓት የሃገሪቷን መንበረ-ስልጣን በኦሮሚያ እምብርት ለመትከል በማለም ፊንፊኔን መቀመጫው ሲያደርግ በርካታ የኦሮሞ ዜጎችን ከመሬታቸው ኣብርሯል።
የኣሁኑ መንግስትም የወረሰውን ከተማ ለማስፋፋት ባወጣው እቅድ ከማሳው ተባርሮ እየተሰቃየ ያለው የኦሮሞ ኣርሶ ኣደር ከቀድሞው ስርዓት በብዙ እጥፍ ይበልጣል። የኦሮሞ ዜጎችን የመኖር መብት ያሳጣውና የኦሮሞ ህዝብን ደግሞ እንድህዝብ ማንነቱን ለማጥፋት ተነጣጥሮ በ21ኛ ክፍለ-ዘመን ውስጥ እየተፈጸመ ያለው ይህ እኩይ ድርጊት፡ ህዝቦች የብሄርና የማንነት መብት እንዲከበርና እንዲጠበቅ እየታገሉ ባሉበት በዚህ ዘመን መፈጸሙ ሁሉም የኢትዮጵያ መንግስታት የኦሮሞ ህዝብን ለማጥፋት ኣቅደው የሚሰሩ መሆኑን ይበልጥ ያስገነዝባል።

የኦሮሞ ህዝብ በሃገሩና ሃብቱ ላይ ኣዛዥ የመሆን መብቱን ከመነፈጉ የተነሳ ከኣንድ ምዕተ-ዓመት በላይ በድህነትና ጭቆና ስር ለመኖር ተገደደ። በባህሉ እንዳይኖር፤ በቋንቋው እንዳይጠቀም ተደረገ። እራሱን ሆኖ በማንነቱ እንዳይታይ፡ የባዕዳንን ማንነት እንዲወርስ የተገደደ ህዝብ ነው። ከመቶ ዓመታት በላይ የቆየው በባህልና ቋንቋው እንዳይጠቀምና በመሬቱና ቀዬው የማፈናቀል ድርጊት ዛሬም እጅግ በከፋና በማንነቱ ላይ ባነጣጠረ መልኩ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። ይህ ድርጊት የኦሮሞ ህዝብ ይበልጥ ለመብቱ እንዲታገል ኣነሳሳው እንጂ ተንበርክኮ እንዲገዛ፤ ጭቆናና ዝርፊያን «እሜን» ብሎ እንዲቀበል ኣያደርገውም።
የኦሮሞ ህዝብ ማንነንቱ ታውቆለት እንዲከበርለት፥ በራሱ ጉዳይ ላይ፡ ወሳኝ መሆኑ እንዲታወቅለት፤ በሃብቱ ላይ ኣዛዥ መሆኑ እንዲረጋገጥለት የሚታገል ህዝብ እንጂ፡ በሌላ ህዝብ ላይ ኣዛዥ የመሆንና በማንነቱ ላይ ጠላታዊ ኣቋም የለውም። በሌላው ህዝብ ሃብት ላይ ፈላጭ-ቆራጭ ሆኖ መጨቆን፡ መዝረፍና ከኣያት-ቅድመኣያቱ መሬት በማፈናቀል የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ዓላማው ኣድርጎ የሚንቀሳቀስ ህዝብ ኣይደለም። የኦሮሞ ህዝብ እየተገደለ፤ እየታሰረና ከቀዬው እየተባረረ ያለው እንደማንኛውም ህዝብ ያለውን መብት በመጠየቁ ብቻ ነው። ይህንን የኦሮሞ ህዝብ ትግል የሚቃወሙትም የራሳቸውንና የቆሙለትን ቡድን ጥቅም የሚሟገቱ ሆድ-ኣደሮችና ጨቋኞች ብቻ እንደሆኑ ጥርጥር የለውም። መብቱ እንዲከበርለት የሚሻ ህዝብ፤ ድርጅትም ሆነ ቡድን የሌላውንም ህዝብ መብት ማክበር ይጠበቅበታል፥ ግዴታውም ነው። ሌላውን ህዝብ በማጥፋት የራስን ህዝብ መብት ማስከበር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና የሚወገዝ ስለሆነ።

በኣሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተራገበ ያለው ትኩስ ኣጀንዳ «Integrated Regional Development Plan (IRDP)» ወይንም በኣጭሩ የተቀናጀ የጋራ ልማት በሚል የወያኔ መንግስት ፊንፊኔን ይበልጥ ለማስፋት ማቀዱን ይፋ በማድረግ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ነው።

ወያኔ ለሃገሪቷና ለህዝብ ከመቀርቆሩ ይህንን እቅድ እንዳወጣ ለማሳመን በተለይም የኦሮሞ ህዝብ እንዲቀበለው ጥረት እያደረገ ነው። ይህ ጉዳይ ከሁሉም በላይ የኦሮሞ ህዝብን ስለሚመለከት የኦሮሞ ህዝብ ከእቅዱ በስተጀርባ ያለውን ድብቅ ዓላማ በጥልቀት መገንዘብ ኣለበት።

ይህ እቅድ ስራ ላይ መዋል ማለት፦
1. የኦሮሞ ህዝብ በገዛ መሬቱ ላይ ለመኖር ያለውን መብት በመንፈግ በእድገትና ልማት ስም መሬቱን እንዲለቅ ተደርጎ ለድህነት ያጋልጣል፤ ቤተሰብ እንዲበተን ያደርጋል። ባዕዳን በኦሮሞ ህዝብ መሬት ላይ እንዲከብሩ ሁኔታ ያመቻቻል። ከመቶ ዓመታት በፊት ተመስርታ እየተስፋፋች ዛሬ በደረስችዋ ፊንፊኔ ከተማ የኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት፤ ከመሬቱ በመፈናቀል እስከዛሬ በህዝቡ ላይ የደረሰውን ድህነትና ውርደት መመልከት ብቻውን በቂ ነው።
2. ኣሁን ኣለ የሚባለውን የይስሙላ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ይበልጥ በማጥበብ ወይንም በመንፈግ ፊንፊኔን ከኦሮሚያ ኣስተዳደር ስር ኣውጥቶ ፌዴራል ኣስተዳደር ስር ያስገባል።
3. በረዥም ዓመታት ትግልና ክቡር መስዋዕትነት ኦሮሞ ያገኛቸውን በቋንቋው የመናገርና የመስራት መብቶች ገፎ ሌላ ቋንቋ እንዲናገር የሱ ባልሆነ ቋንቋ እንዲሰራ ያስገድደዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ ያገኛቸውና በአገሪቷ ህገ-መንግስት እንኳ የተቀመጡትን «ሁሉም ብሄሮች፥ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ የመጠቀም፥ እንዲሁም ባህልና ታሪካቸውን የማሳወቅና የማሳደግ መብት ኣላቸው» የሚለውን በመቃረን፡ ኦሮሞ በባህሉ እንዳይኖር፡ እንዳያሳድግና ባህሉን እንዳያስጠብቅ መንገድ ይዘጋበታል።
4. የኦሮሞ ህዝብ/ኦሮሚያ ወደ ፊንፊኔ ለመደባለቅ ከታቀዱት ኣካባቢዎች የሚያገኘውን የኢኮኖሚ ገቢ ኣሳጥቶ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና ያሳድራል።

5. የኦሮሞ ህዝብ በእድገት ስም በሚወሰድ እርምጃ ተገልሎ መሬቱን የተቀራመቱትና የሰፈሩትን ባህልና ቋንቋ እንዲወርስ በማስገደድ የኦሮሞ ማንነት(ኦሮሙማን) ያጠፋል።

6. በልማት ስም የሚወሰዱት እነዚህ እርምጃዎች ሁሉ ኣካባቢን በመበከል የኦሮሞ ህዝብን መጻኢ ህይወት ጥያቄ ውስጥ ያስገባሉ።

7. በመሪር ተጋድሎ ኣንድነቱን ያረጋገጠውን የኦሮሞ ህዝብ በምስራቅና ምዕራብ በመከፋፈል የህብረት ሃይሉን በማላላት የባዕዳንን የጭቆና ኣገዛዝ ለማሰንበት በር ይከፍታል።

8. ቀስ በቀስ በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ሌሎች ከተሞችንም እየዋጠ ሄዶ የኦሮሞ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች ተውጦ ማንነቱ እንዲጠፋ መንገድ ይጠርጋል። ከነዚህም ሌላ በርካታ ነጥቦችን መዘርዘር ይቻላል።
የኦሮሞ ህዝብን በማፈናቀል ፊንፊኔን ለማስፋት ታቅዶ እየተሰራ ያለው ስራ በጨቋኙ የሚኒሊክ ዘመን የተጀመረ እቅድ ቀጣይ ኣካል ነው። ይህ የረዥም ዓመት እቅድ ከኦሮሞ ህዝብ ባለመገታታ በኦሮሞ ላይ ያደረሰውን ጉዳት መገንዘብ ኣያዳግትም።
ባዕዳን እንዳሻቸው ተንፈላስሰውበት የሚኖሩባት ፊንፊኔ እውን የሆነችው የኦሮሞ ህዝብን በማፈናቀል ለመሆኑ ከጉለሌ፤ ኤካ፤ ለገ-ጣፎ፤ ለገ-ዳዲ፤ ኣቃቂ፤ ሰበታ ፤ ሱሉልታና ከሌሎችም ኣካባቢዎች በገዢ የኢትዮጵያ መንግስታት ተፈናቅሎ እንደ 2ኛ ዜጋ በመቆጠር፡ በድህነት ኣረንቋ ውስጥ በመዘፈቅ፡ ቤተሰቡ ተበትኖና ኣስከፊ ህይወት እየመራ ያለውን የኦሮሞ ህዝብ መመልከት በቂ ይሆናል።

ስለሆነም ይህንን ሃገሪቷ ትተዳደርበታለች የሚባለውን ህገ-መንግስት እንኳ የጣሰ፡ የኦሮሞን ህዝብ ኑሮ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ፡ ህዝቡ ለነጻነቱ የሚያደርገውን ትግል ለማራዘም ወይንም ኣፍኖ በማስቀረት ባዕዳን እንዲፈነጩበት ማድረግን ያለመው እርምጃ ሊወገዝና ሊቃወሙት የሚገባ ነው። ለህዝብ ካለው ንቀትና እራሱን ከህግ በላይ ኣድርጎ ከማየት ወያኔ የሚወስደው ይህ እርምጃ የኦሮሞ ህዝብን ማንነት ለማጣፋት በስልት እየተካሄደ ያለ ስለሆነ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለዲሞክራሲ፤ ለህዝቦች እኩልነትና ለሰብዓዊ መብት የሚታገሉ ኣካላት ሁሉ ሊቃወሙትና ሊያወግዙት ይገባል።

በተለይም ደግሞ የጉዳዩ ባለቤት የኦሮሞ ህዝብ ይህንን እሱን ለማጥፍት ኣልሞ በህዝብ ጸሮች የወጣውን እቅድ ኣንድነቱን ኣጠናክሮ በቆራጥነት ከመጋፈጥ በስተቀር ሌላ መፍትሄ እንደሌለ መገንዘብ ኣስፈላጊ ይሆናል። ይህ እቅድ ሙሉ በሙሉ እንዲከሽፍ እየታገሉ ኣጠቃላይ መፍትሄ ለሆነው የኦሮሚያ ሉዓላዊነት ትግልን ለማፋፋም መንቀሳቀስ ከኦሮሞ ህዝብ ይጠበቃል።

የኦሮሞ ህዝብን ለከፋ ጉዳት በመዳረግ ለራሳቸው እድገትን የመመኘት የጨቋኞች የዘመናት ኣካሄድ በኣሁኑ ትውልድ ፍጻሜ እንዲያገኝ መስራት የዜግነት ግዴታ ነው!!

ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኢንፎ-ዴስክ

Check Also

faannoo

OROMO CIVILIANS CONTINUE TO BE TARGETED BY FANO MILITIA

Amhara Fano continued to attack Oromo civilians. In this latest incident, at least 17 people …